ለሴቶች አስፈላጊ የምንለው የንፅህና አጠባበቅን መረዳት
በኩዊር ሴቶች ዘንድ ባህል ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው የንፅህና አጠባበቅ በጤና ባለሙያ መነፅር ሲቃኝ | በአቢጌል የተፃፈ
1 ለሴቶች አስፈላጊ የምንለው የንፅህና አጠባበቅን መረዳት
የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ሴቶች ከተቃራኒ ፆታ አፍቃሪዎች (በተለምዶ ቀጥ ከምንላቸው) የሚለያዩ ወሲባዊ ልምድ እና ተግባራት አላቸው እናም በግንኙነት ወቅትም ሆነ ከግንኙነት በኋላ ንፅህናችንን መጠበቅ አለብን።
የመከላከያ ዘዴዎች(Barrier methods) በግንኙነት ወቅት የጥርስ መከላከያዎችን(dental dam) ማድረግ ፣ ጓንቶች እና በሰው ሰራሽ የቁላ አሻንጉሊት(Dildo) ላይ ኮንዶምን መጠቀም ወይም ከግንኙነት በፊትም ሆነ በኋላ ማጠብ የአባላዘር(STI) በሽታዎችን ስጋትን ለመቀነስ አስፈላጊ ናቸው።
የተለያዩ እቃዎችን በጋራ አለመጠቀም የተጋሩ የወሲብ አሻንጉሊቶች(dildo) ፣ የውስጥ ሱሪ ወይም መላጫዎች በተመለከተ የበለጠ ጥንቃቄ ሊኖራቸው ይገባል ከቻልን እነዚህን ነገር በጋራ አንጠቀም።
ባክቴሪያ ለመከላከል የሴቶች ብልት በተፈጥሮ አሲዳማ ነው በመሆኑም የQueer ሴቶች ወሲብ አዲስ ባክቴሪያዎችን ወደ ብልት አካባቢ (እጆች፣ ከአፋዎች ፣ ወይም ከአሻንጉሊት) ማስተዋወቅ ፣ የሴት ልጅ ብልት ውስጥ ያለውን አሲድ ተመጣጣኝ እንዳይሆን በማድረግ ለተለያዩ ባክቴሪያዎች እንድንጋለጥ ያደርገናል በመሆኑም በግንኙነት ወቅት የምንጠቀማቸውን ነገሮች ንፅህና በመጠቅ የአጋራችንንም የኛንም ጤንነት እንጠብቅ።
ጠቃሚ ምክር: - በውሃ መታጠብ ባንችል እንኳን ሌሎች የንፅህና መጠበቂያዎችን(Alcohol free wipes) እንጠቀም
2. ዕለታዊ አካል እና የቆዳ ንፅህናን መጠበቅ
የምንጠቀማቸው ደረቅም ሆነ ፈሳሽ ሳሙናዎችን እንዲሁም ቅባት(lotion) መምረጥ ፣ ከቆዳችን ጋር አብሮ ሚስማማውን መጠቀም እንዲሁም ገላችንን በምንታጠብ ግዜ የመራቢያ አካላችንን በሳሙና አለመታጠብ በተለይ መዐዛ ባላየው ሳሙናዎች ባንጠቀም ይመረጣል።
ለላብ የተጋለጡ አካባቢዎችን ከሌሎች አካላችን በተለየ በደንብ ማፅዳት ለምሳሌ በጡቶች ውስጥ እና ጡታችንን ከፍ በማድረግ ከስሩ ፣ ከጉልበታችን ስር መታጠፍያውን ፣ ጭኖቻችን መካከል ፣ ብብታችን ስር እና አንገታችን ስር በደንብ መታጠብ
የማድረቂያ ፎጣዎች : ሁል ጊዜ ንጹህ, ደረቅ ፎጣ መጠቀም በሳምንት ቢያንስ 2 ጊዜ ይለውጡ።
3.የሴት ብልት ጤንነትን እና ጽዳት መጠበቅ
በተፈጥሮ የሴት ልጅ የውጭኛው መራቢያ አካል ንፁህ ባለመሆኑ ንፅህናውን መጠበቅ አለብን ፣ ነገር ግን የውስጠኛው ክፍል(ብልት/vagina) ንፁህ በመሆኑ ምንም አይነት መሳሪያ(douching) በመጠቀም ማፅዳት የለብንም!!
እነዚህን ማፅጃዎች (douching)መጠቀም ኢንፌክሽኖችን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ስለዚህ የውጫዊውን መራቢያ አካላት ብቻ እናፅዳ ለሱም መአዛ ያለው መፀዳጃ አንጠቀም።
የውስጥ ሱሪ(pants) ከጥጥ የተሰሩ ፓንቶችን መጠቀም እና እርጥበት ወይም ላብ የውስጥ ሱሪ ውስጥ እንዳይኖር መከላከል ይሄንንም ምናደርገው በየቀኑ የውስጥ ሱሪዎችን በመቀየር ነው (ሙቀቱ ለባክቴሪያዎች እና ፈንገሶች ምቹ የሆነ መኖሪያን ይፈጥራል)። እንዲሁም ለሊቱን ፓንት ሳናደርግ በማደር ውጫዊው የመራቢያ አካል በቂ አየር እንዲያገኝ ማድረግ የተሻለ ነው(እንደየሰዉ ፍላጎት)።
4. የሴት ብልት ሽታ መከላከል
ንፅህናን መጠበቅ + በቂ ውሃ መጠጣት + አመጋገብን ማስተካከል የሴት ብልት እንዳይሸት እና ማራኪ ጠረን እንዲኖረው ማድረግ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላል።
ጠረን ያላቸው ምርቶችን አለመጠቀም - እነዚህ ምርቶች ተፈጥሯዊውን ጠረን በመረበሽ ብልታችን መጥፎ ጠረን እንዲኖረው ያደርጋሉ።
አዘውትሮ መታጠብ - በየቀኑ እና በምንፀዳዳበት ወቅት ብልትን መታጠብ የውስጥ ሱሪዎችን እና ሞዴሶችን በተቻለ ፍጥነት መቀየር።
ማስጠንቀቂያ - ከበድ ያለ ሽታ ፣ ማሳከክ ፣ ወይም ያልተለመደ ፍሰት ካስተዋልን የባክቴሪያ ወይም ሌላ ኢንፌክሽን ሊሆን ይችላል እና በአቅራቢያዎ ወዳለ ጤና ጣቢያ በመሄድ ባለሞያዎችን ያማክሩ ‼
5. ሚወገዱ ነገራቶች - ፀጉር እና ጥፍር
የመራቢያ አካላት ፀጉር - መላጨት ፣ መቁረጥ ፣ መላጥ (waxing) ወይም ተፈጥሮአዊ ይሁኑ ብለን መተው (ግን ባንተወው ይመረጣል )እንችላለን ዋናው ንፁህ ማድረግን አንርሳ በተጨማሪም ስናስወግዳቸው ንጹህ መሳሪያዎችን እንጠቀም እንዲሁም ስለታማ ማስወገጃዎችን ከአጋራችን ጋራ ቢሆንም ማጋራት እናቁም።
የጥፍር ንፅህና - ጥፍሮቻችን በአግባቡ ካላፀዳን እና ካልቆረጥን የተለያዩ ጀርሞችን ይይዛሉ ስለዚህ ባክቴሪያዎቹ ወደ ግንኙነት አጋራችን እንዳይሄዱ ብናፀዳቸው ይመረጣል እንዲሁም አካላት እንዳይቧጨሩ ብንቆርጣቸው የተሻለ ነው።
ከላጨን በኋላ በአከባቢው እንዳይበላን በደንብ ደግመን ማጠብ እንደ አማራጭ መውሰድ እንችላለን።
6. ከግንኙነት በፊትም ሆነ በኋላ አፋችንን እናፅዳ
ከግንኙነታችን በፊት ጥርሳችንን በጥርስ በሳሙና መቦረሽ ወይም መጉመጥመጥ የባክቴሪያ ስርጭት እንዳይሰራጭ ለመከላከል እንደገና አጥብቆ አፍን መጉመጥመጥ ወይ መታጠብ በተለይም የአፍ እና ብልት ግንኙነት(lick sex )ካደረግን በኋላ።
7. አንሶላ እና የትራስ ጨርቅን ንፅህናን በመጠበቅ አልጋችንን ማስዋብ እና ማንፃት
በየሳምንቱ መቀየር - ላብን ጨምሮ ከሰውነታችን የሚወጡ የተለያዩ ፈሳሾች አንሶላዎቻችን ላይ የተለያየ ባክቴሪያ እንዲኖር ያደርጋሉ እነዚም ባክቴሪያዎች ወደኛው ሰውነት ሊተላለፉ እና ለተያየ ኢንፌክሽን ሊዳርጉን ስለሚችሉ በየሳምንቱ ማጠብ እና መቀየር አስፈላጊ ነው።
ንፁህ ፎጣ ማንጠፍ - በወሲብ ወቅት የሚፈሰንን ፍሳሽ ለመከላከል ሌላ ንፁህ ፎጣ በአንሶላው ላይ ማንጠፍ በተለይም የወር አበባ ላይ ተሆኖ በሚደረግ ወሲብ እና የሰው ሰራሽ ቁላ አሻንጉሊቶችን (Dildo) በመጠቀም የሚደረጉ ወሲባዊ ግንኙነቶች ላይ ንፁህ ነገር ማንጠፍ ይመረጣል።
የቤት እንስሳት(pets) - በእቤት ውስጥ እንደ ድመት እና ውሻ ያሉ ለማዳ የቤት እንስሳት ካሉ ፣ ፀጉራቸው በቀላሉ ረጋፊ እና አንሶላው ላይ የሚቀር በመሆኑ በተደጋጋሚ መቀየሩ የተሻለ ነው።
8. ከፖንት በላይ ሚቀመጡ(panty liner) የንፅህና መጠበቂያችን መጠቀም
ፓንት ሊነሮችን መጠቀም ከመራቢያ አካላችን ሚወጡ ፈሳሾችን መጦ በመያዝ አቅራቢያውን ደረቅ እና ምቹ ያደርጉልናል ነገር ግን ከጥጥ የተሰሩ እንደመሆናቸው ሙቀትን በመፍጠር ለባክቴሪያ ምቹ አከባቢን እንዳይፈጥሩ ወዲያው መቀየርን አንዘንጋ ፣ ከ 12 ሰዐት በላይ ማቆየት የለብንም።
ከግንኙነት ወይም አካላችንን ከሚፈትኑ እንቅስቃሴዎች በኋላ ሰውነታችንን መታጠብ።
በቂ ውሃ መጠጣት - ለሰውነታችን ተመጣጣኝ የሆነ ውሃ በጠጣን ቁጥር ፣ ከሰውነታችን ውስጥ መውጣት ያለባቸው ቆሻሻዎችም ተመጣጣኝ ሆነው ይወጣሉ።
9. መጠቀም እና ማስወገድ ያሉብን ምርቶች
መጠቀም ያሉብን ምርቶች
ከሽታ ነፃ የሆኑ የሳሙና ማጽጃዎችን መጠቀም በተለይ ስስ(sensitive)ለሆነ ቆዳ
ብዙ ኬሚካል ወይም ምንም ኬሚካል የሌለው የጥርስ ሳሙናዎችን መካከለኛ ልስላሴ ካላቸው የጥርስ ቡርሾች ጋር መጠቀም ፣ በቀን ሁለቴ (ጠዋት እና ማታ) ጥርሳችንን እና ምላሳችንን ሁሌም ማፅዳት ፤ በተለይ ምላሳችንን ማፅዳት እንዳንረሰ።
የብብት ሽቶዎች (Roller or deodorant) መጠቀም
❌ መጠቀም የሌለብን ምርቶች
ጠረን ያላቸው የብልት ሽቶዎች(vaginal spray) ፣ ውስጣዊ ማፅጃዎች (vaginal douching) ፣ አልኮላማ የሆኑ ዋይፕሶች(alcoholic wipes) ፣ የመራብያ አካላቶችን በአረፋማ ሳሙና መታጠብን እና የመሳሰሉትን አለመጠቀም።
ማሳሰቢያ - ለቆዳችን የምንጠቀማቸውን ምርቶች ፋርማሲ ሚሰሩትን ባለሞያዎች በማማከር ወይም ከማህበራዊ ሚዲያ በማፈላለግ ከቆዳችን ጋር ሚስማማ ብንገዛ የተመረጠ ነው።
10. ጡታችንን መመልከት (breast self-examination)
ጡታችንን የወር አበባችን በመጣ ከ3 - 7 ቀን ውስጥ እራሳችን በቤታችን ሆነን መመርመር።
እንዴት...?
ከመስታወት ፊት በመቆም ሁለቱንም ጡታችንን መመልከት ፣ በተፈጥሮ አንደኛው ጡታችን ከሌላኛው በመጠን ሊያንስ/ሊበልጥ ይችላል ነገር ግን በአከባቢው የመቅላት ወይ የሽፍታ ምልክት ካለ መመልከት ።
የጡታችንን ጫፍ በመያዝ ቁስል ካለው እና ከውስጡ የሚወጣ ፈሳሽ ካለ መመልከት ፣ ውሀ ሚሙስል ንፁህ እና መግል ሚሙስል ነጭ ፈሳሽ ካለው ወደ ጤና ተቋም መሄድ ይኖርብናል።
በጣቶቻችን ጡታችንን ዙሪያውን እና ብብታችን ስር(arm pit) ድረስ ጫን እያልን መፈተሽ በተለይ ሰውነታችንን በምንታጠብበት ወቅት ቢሆን ይመረጣል ፤ በዚ ወቅት ያልተለመደ(ያልወለደችች ሴት በተፈጥሮ ጫፎቹ አከባቢ ጠጠር ያለ ነገር አላት) ጠጠር ብሎ ያበጠ እና የማይንቀሳቀስ ነገር እና ህመም ከተሰማን በአቅራቢያችን ወዳለ ጤና ጣብያ እንሂድ።
ጡታችንን በየወሩ በዚ መልኩ መፈተሽ አስፈላጊ ነው በተለይም በቤተሰብ ውስጥ ከዚህ ቀደም በእንደዚ አይነት ሁኔታ ውስጥ ያለፈ ሰው ካለ እና የወር አበባችን እየተዘበራረቀ የሚመጣ ከሆነ ፤ ይህ እራስን ፍተሻ(self-examination) ለምን አስፈለገን?
1. የጡት ካንሰር ህመም ስር ሳይሰድ ወዲያው ለማግኘት እንዲሁም ህክምናውን ወዲያው በመጀመር የተሻለ ውጤት ለማግኘት
2. አብዛኛው የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ሴቶች ስለማልወልድ እና ስለማላጠባ ችግር የለውም ብለው ሊዘናጉ ይችላሉ ነገር ግን ይህ ልክ አይደለም እንደውም አለመውለድ እና አለማጥባት የጡት ካንሰር እንዲፈጠር ከሚያደርጉ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ነው(ነገር ግን በጣም በዝቅተኛ ሁኔታ ነው ይሄ ምክንያት ሚሆነው)
3. አብዛኛው በሚባል መልኩ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ሴቶች የአልኮል መጠቶች እና የሲጋራ ወይም ሌላ ዕፆች ተጠቃሚ ናቸው ይሄም በከፍተኛ ደረጃ ለጡት ካንሰር መንስኤ ነው
4. በየወሩ ጡታችንን በምንመለከትበት ጊዜ ጡታችንን በደንብ ማወቅ እንችላለን እናም የሆነ የተለየ ነገር ሲፈጠር በቀላሉ እንድናውቅ ያስችለናል
5. በሀገራችን ኢትዮጰያ አብዛኛው ሴቶች እየተጠቁበት የሚገኙት ህመም ነው ይኸውም በቁጥር ስናስቀምጠው ወደ 30% ሊጠጋ ወይም ሊበልጥ ይችላል ከነዚህም ውስጥ 70% ቆይተው ስለሚመረመሩ ከፍተኛ እና ለህይወታቸው አስጊ ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው ሚያውቁት ለዚም ምክንያቱ በቂ ግንዛቤው አለመኖር ፣ በየወሩ እራስን ካለመመርመር ወይ ነገሮችን ችላ ማለት ነው።
አንድ ማወቅ ያለብን ነገር እራሳችንን በየወሩ መፈተሻችን 100% እርግጠኛ ሆነን ህመሙ የለብንም እንድንል አያስችለንም ስለሆነም
በቤተሰብ ውስጥ(በተለይ እናት ፣ ሴት አያት እና እህት) እንደዚ አይነት ሁኔታ ውስጥ ያለፈ ሰው
እድሜዋ ከ35 አመት በላይ የሆነች እንስት
የመጀመሪያው የወር አበባዋ ከ12 አመት በፊት የተመለከተች እና ከ55 አመት በኋላ ሚፈሳት ሴት(በተለምዶ እሰከ 55 አመቷ ያላረጠች ሴት)
ሆርሞን ህክምና(hormonal therapy) የምትወስድ ሴት በተለይ ኢስትሮጂን ምትጠቀም(ተጠቅማ የነበረች) ሴት ከፍተኛ የመያዝ እድል አላት
ስለዚህ ከአልኮል እና ከተለያዩ ሲጋራዎች ወይም ዕፆች እራሳችንን በማራቅ ጤናችንን እንጠብቅ !! በነገራችን ላይ ከነዚ ነገሮች መራቅ ያለብን ለጡታችን ብቻ ስንል አይደለም ለመላው አካላታችንም ጭምር ነው አብዛው ካንሰራዊ እና ገዳይ በሽታ መንስኤው ይህ ነውና!!
አቢጌል ✍️✍️✍️




